ታሪክ
አወቃቀር
አፈ-ጉባኤዎች
አባላት
የስነምግባር ደንብ
ሥልጣንና ተግባር
ህጋዊ መሠረቶች
ህግ መንግስት
ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 251/1993
የስብሰባና የስነስራት ደንብ
ሌሎች
ቋሚ ኮሚቴዎች
አባላት
የስነምግባር ደንብ
ውሳኔ ያገኙ ጉዳዮች 
ህገመንግስታዊ ትርጉም 
የህገመንግስትና የክልል ጉዳዮች
የገቢዮችና ድጎማ ጉዳዮች
ሌሎች
በሂደት ላይ ያሉ ጉዳዮች
ስትራቴግክ እቅድ
ቃለ-ጉባኤ
ሪፖርት
ህትመቶች
ፎርሞች
ዜና
ጨረታ
ማስታወቂያ
መልስ
የፎቶ ማህደር
ጠቃሚ አድራሻዎች
 

የተከበራችሁ የምክር ቤት አባላት!

 በመጀመሪያ ለ3ኛው የምክር ቤቱ የሥራ ዘመን 2ኛ የሥራ ጊዜ ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባ እንኳን በሠላም መጣችሁ እያልኩ የምክር ቤቱን አጠቃላይ የሥራ ክንውን አጭር ሪፖርት ለማቅረብ እንዲፈቀድልኝ እጠይቃለሁ፡፡

 እንደሚታወቀው አንደኛ መደበኛ ስብሰባችንን ባካሄድንበት ወቅት የምክር ቤታችንን የቀጣይ ዓመት የትኩረት አቅጣጫዎች መጠቆማችን የሚታወስ ነው፡፡ እነኝህን መሠረታዊ አቅጣጫዎች መነሻ በማድረግ የምክር ቤቱን የአምስት ዓመት መርሃ-ግብር ባገናዘበ ሁኔታ ዝርዝር ዓመታዊ ዕቅድ ወጥቶ በርካታ ሥራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል፡፡ ዓመታዊ ዕቅዱም በተቻለ መጠን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የተሰጡትን ተግባርና ኃላፊነቶች በሚያሳካ መልኩ የተዘጋጀ ሲሆን በዋነኛነት የምክር ቤቱን አቅም የማጠናከር፣ በሕዝቦች መካከል ዲሞክራሲያዊ አንድነት ሥር እንዲሰድ የማድረግ፣ መንግሥት ከሚመድበው ሀብት ሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ እኩል ተጠቃሚ እንዲሆን የሚያስችል ፍትሐዊ የድጐማ ቀመር ማዘጋጀትና ሌሎችም ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን የሚያጠናክሩ ተግባሮች ተከናውነዋል፡፡

 ከላይ የተጠቀሱትን ዋነኛ ተግባሮች መሠረት በማድረግ ምክር ቤቱ ኃላፊነቱን ለመወጣት በሚያስችሉ በሥሩ በተደራጁ ሁለት ቋሚ ኮሚቴዎችና በድጋፍ ሰጪ ጽ/ቤት ባለሙያዎች በመታገዝ ሥራውን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ ስለሆነም ዛሬ የሚቀርበው ሪፖርት ዘንድሮ ለማከናወን በዕቅድ የያዝናቸውንና በሂደት ላይ የሚገኙትንም ሥራዎች የሚዳስስ ከመሆኑም በላይ ምክር ቤቱ በቀሩት ጊዜያትና በ2000 ዓ.ም. ሊያከናውናቸው ያቀዳቸውን ተግባራትና የትኩረት አቅጣጫዎችንም በአጭሩ ያመላክታል፡፡

 ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሕገ-መንግሥታዊ ሥልጣኑን መሠረት በማድረግ የሕዝቦችን ዲሞክራሲያዊ አንድነት ለማጠናከር የሚያስችሉ ዕቅዶችን ይዞ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ በዚህ ረገድ አንደኛ መደበኛ ስብሰባችንን ካካሄድን በኋላ ከተከናወኑት ተግባራት በቀዳሚነት የሚጠቀሰው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ነው፡፡ ይህ በዓል በመላው ሀገራችንና በውጭ ሀገር በሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ዘንድ በተለያዩ ዝግጅቶች በደማቅ ሁኔታ መከበሩ ለብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ማንነት የተሰጠውን ትኩረት በሚገባ ያረጋገጠ ነው፡፡ ይህ ታሪካዊ በዓል በአገር አቀፍ ደረጃ አዲስ አበባ ላይ በተለያዩ ኘሮግራሞች የተከበረ ሲሆን በዋዜማው የተካሄዱት ያለፉትን ዓመታት የሀገራችን የፌዴራሊዝም ጉዞ የገመገመ ሲምፖዚየምና የህዝቦችን ባህላዊ ገጽታ የሚያንፀባርቅ ኢግዚቪˇን እንዲሁም በዕለቱ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦችን ማንነት አስመልክቶ የተደረገው ሁሉ ዓቀፍ የልምድ ልውውጥ የመልካም ጅማሬው መገለጫዎች ናቸው፡፡  

 በዓሉ ከኢትዮጵያ ውጪም በሀያ ሀገሮች የተከበረ ሲሆን በዚያ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እንዲገናኙ በር የከፈተ ነው፡፡

 በአጠቃላይ ሕገ-መንግሥታችን የፀደቀበት ህዳር 29 ቀን የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ሆኖ ሲከበር በአሉ የተሳካ እንዲሆን ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላደረጉት የምክር ቤቱ አባላት፣ የክልል መስተዳድሮችና ምክር ቤቶች፣ በተለይም ለአዲስ አበባ ጊዜያዊ ባለአደራ አስተዳደር ምሥጋናችንን እናቀርባለን፡፡

 የአዲስ አበባ ጊዜያዊ ባለአደራ አስተዳደር ከነበረው የላቀ ድርሻ ጋር በከተማው ትልቁንና ውድ የተባለውን የጐተራ ተላለፍ መንገድ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች አደባባይ እንዲሆን በመሰየሙ፣ ከሚሊንየም በዓል ጋር በተያያዘም የመስተዳድሩ የሚሊንየም ፅ/ቤት በዚህ አደባባይ ላይ የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦችን አንድነት፣ ህብረት፣ ፍቅርና መቻቻል የሚያንፀባርቅ ሀውልትና ፋውንቴን ለማሰራት ዕቅድ በመያዙ እንዲሁም የፌዴሬሽን ምክር ቤትም የራሱን ግብአት እንዲያደርግ በመጠየቁ በዚህ ረገድ አደባባዩን ከማስተዋወቅ ጀምሮ የበኩላችንን እንድናደርግ በዚህ አጋጣሚ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡

 የተከበራችሁ የምክር ቤት አባላት!

 ህገ-መንግሥታችን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ከማዕከላዊ መንግስት ለክልል መንግሥታት የበጀት ድጋፍ የሚሰጥበትን ቀመር ማዘጋጀት እንደሚኖርበት ይደነግጋል፡፡ በዚህ መሠረት ቀደም ሲል በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ተዘጋጅቶ ሲቀርብ የነበረውን የበጀት ድጐማ ማከፋፈያ ቀመር መሠረተ ሐሳቡን ለማስጨበጥ በየደረጃው ግንዛቤ ለመፍጠር የተደረገ ጥረት መኖሩ የሚታወቅ ነው፡፡ ይሁንእንጂ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ሲቀርብ የነበረው አዲሱ የበጀት ድጐማ ቀመር ከመርህ አንፃር ተቀባይነት ቢኖረውም የተወሰነ ውስንነት እንዳለው ስለታመነበት በሁሉም ዘንድ እኩል ተቀባይነት ባለማግኘቱ እንደገና በፌዴሬሽን ምክር ቤት ፅ/ቤት ሥር በሚዋቀረው የባለሙያ ቡድንና በምክር ቤቱ የቅርብ ክትትል እንዲሠራ የምክር ቤቱ አባላት መወሰናቸው የሚታወስ ነው፡፡

 ይህንኑን የምክር ቤቱን ውሳኔ መነሻ በማድረግ በቀዳሚነት ጠንካራ አካል ወይም ተቋም ለማደራጀት ሠፊ ጥረት ተደርጓል፡፡ ይህ ተቋም እስከሚመሰረትም የምክር ቤቱ ፅ/ቤት ባለው ውስን ባለሙያ ሥራውን በመጀመር በሂደት እንዲዳብር በወሰዳቸው አማራጮች በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤታማ ሥራ ሊሠራ ችሏል፡፡

 የቀመሩ ዝግጅት ግልፅነት እንዲኖረውና የክልሎችንም ተሳትፎ በቀጥታ ለማረጋገጥ ሲባል ከተለያዩ ክልሎች የተውጣጡ ባለሙያዎችን በማደራጀት የተደረገው ጥረት መረጃዎችን በማሰባሰብና በተጨባጭ የክልላቸውንም ሁኔታ በመግለፅ በኩል ጠቃሚ አካሄድ እንደነበረ ለማረጋገጥ ችለናል፡፡ እነዚህ ከየክልሉ የተውጣጡ ባለሙያዎች በፅ/ቤቱ ከሚገኙ ባለሙያዎች ጋር በመሆን ወደ ተለያዩ ክልሎች ተሰማርተው መረጃዎችን ለማሰባሰብ እንዲችሉ አስፈላጊውን የአቅም ግንባታ ሥልጠና ካገኙ በኋላ የአሠራርና የአካሄድ ሥልት በመቀየስ አዲሱ የበጀት ቀመር የሚከለስበት ሁኔታ ላይ አቅጣጫ እየተሰጣቸው ውጤታማ ሥራ አከናውነዋል፡፡

 በዚህ መሠረት አዲሱ የቀመር ዝግጅት ሥራው ሁሉንም ባለድርሻዎች ባሳተፈ መልኩ እንዲከናወን በማድረግ ተአማኒነትንና ግልፅነትን ለመፍጠር ጥረት ተደርጓል፡፡

 ዲሱ የበጀት ማከፋፈያ ቀመር ዝግጅት እንዲሳካ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር፣ የ DSA ኘሮጀክት ፅ/ቤት፣  GTZካናዳ የሚገኘው ፎረም ኦፍ ፌዴሬሽን እና የዓለም ባንክ ልምዳቸውን በማካፈልና በማቴሪያል አቅርቦት አስፈላጊውን ድጋፍ የሰጡን ሲሆን፣ ከክልሎች የተገኘው መረጃ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ዋነኛ ምንጭ ተደርገው የተወሰዱት የፌዴራል መሥሪያ ቤቶች ናቸው፡፡

 እንደሚታወቀው የበጀት ድጐማ ቀመር ዝግጅት አንድ ጊዜ ተሠርቶ የሚያበቃ ሳይሆን በየጊዜው የተለያዩ አዳዲስ አመልካቾችን በመጨመር እየተሻሻለ የሚሄድ በመሆኑ ከግምታዊ የበጀት ክፍፍል ወደ ተሻለ ፍትሐዊ የቀመር ዝግጅት መሸጋገራችን ለሀገራችን ልማትና ለህዝቦች ተቻችሎ መኖር ወሳኝ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ ለመግለፅ እወዳለሁ፡፡       

 የዚህ ጥናት ውጤት ለበጀት ድጐማና የጋራ ገቢዎች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ የቀረበ ሲሆን ኮሚቴውም የተወያየበትን የውሳኔ ሐሳብ ለምክር ቤቱ ጉባኤ በዛሬው ዕለት በማቅረብ እንደሚያስወስን ይጠበቃል፡፡

 በሌላ በኩል በህገ-መንግሥታችን መሠረት ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ከተሰጡት ስልጣንና ተግባራት አንዱ በህዝቦች እኩልነትና በመፈቃቀድ ላይ የተመሠረተ አንድነት ሥር እንዲሰድና እንዲዳብር ማድረግ ነው፡፡ ይህንን መሠረተ ሀሳብ ተግባራዊ ለማድረግ እያንዳንዱ ብሔር፣ ብሔረሰብና ህዝብ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ውስጥ ቢያንስ አንድ ውክልና ሊኖረው እንደሚገባም ህገ-መንግሥቱ ይደነግጋል፡፡

 ይሁንእንጂ እስከአሁን ድረስ በምክር ቤቱ ውስጥ ውክልና ያገኙት ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ብዛት 67 ብቻ ናቸው፡፡ ሌሎችም እየተጠኑ ውክልና ማግኘት ህገ-መንግሥታዊ መብታቸው ስለሆነና ምክር ቤቱም ባለፈው ጉባኤው ይኸው እንዲከናወን ባሳለፈው ውሣኔ መሠረት የጽ/ቤታችን ባለሙያዎች ከክልል ምክር ቤቶች ጋር በመተባበር በዚህ ዙሪያ ጥናት አካሂደዋል፡፡ በጥናቱ መሠረት አስር የሚሆኑ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች መስፈርቱን ያሟላሉ የሚል ግምት በመኖሩ የጥናቱ ውጤት ለህገ-መንግሥትና ክልል ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ቀርቦ ውይይት ተደርጐበታል፡፡ የኮሚቴው የውሣኔ ሀሳብ ዛሬ ለተከበረው ምክር ቤት ለውሣኔ የሚቀርብ ይሆናል፡፡

 በተጨማሪም የምክር ቤቱን አሰራር ለማጠናከር ግልጽነትና ተጠያቂነት እንዲኖር የሚያስችል የአባላት የአሰራር፣ የአደረጃጀትና የስብሰባ ስነስርዓት ደንብ ተዘጋጅቶ በህገ መንግስትና ክልሎች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ውይይት የተደረገበት ስለሆነ እሱም ለዚሁ ም/ቤት ቀርቦ ውሳኔ እንደሚያገኝ ይታመናል።

 የተከበራችሁ የምክር ቤት አባላት!

 ለዚህ ዓመት ከያዝናቸው ዕቅዶች ውስጥ ዋነኛው የአቅም ግንባታ ሥራ ነበር፡፡ በዚህ ዙሪያ የምክር ቤቱን ፅ/ቤት መልሶ ለማደራጀትና በሰው ኃይል ለማጠናከር የተከናወኑ ተግባራት ቢኖሩም የምክር ቤቱን አባላት አቅም ከማሳደግ አኳያ የሚቀሩ ሥራዎች መኖራቸው በግልፅ የሚታወቅ ነው፡፡ አዲሱን የበጀት ማከፋፈያ ቀመር ለሚያዘጋጁት ባለሙያዎች በሁለት ዙር ሥልጠና የተሰጣቸው ሲሆን የፅ/ቤቱም ኃላፊዎችና ሠራተኞች በስቪል ሰርቪስ ማሻሻያ ኘሮግራም ዙሪያ ተቋማዊ ለውጥ ለማምጣት አቅማቸውን እንዲያዳብሩ ሥልጠና ሲሰጣቸው ቆይቷል፡፡ በአሁኑ ጊዜም ወደ ተግባር ለመለወጥ ጥረት በመደረግ ላይ ይገኛል፡፡

 በዓመታዊ ዕቅዱ ትኩረት የተሰጠው ሌላው ተግባር ለቀጣይ ትውልድ የሚተላለፍ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን ዲሞክራሲያዊ አንድነትና ማንነት የሚያንፀባርቅ ጥልቀት ያለው ጥናት ተካሄዶ መረጃውን አደራጅቶ የማቆየት ጉዳይ ነው፡፡ ይህንን ጉዳይ በተመለከተ የምክር ቤቱ ፅ/ቤት የተለያዩ ዘዴዎችንና ሥልቶችን በመጠቀም በተሻለ ሁኔታ በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡

 በሌላ በኩል የዲኘሎማሲ ሥራን በተመለከተ ሀገራችን ባለፉት አራት ዓመታት ያስመዘገበችውን ዕድገትና የወደፊት ራዕይ እንዲሁም የሻዕቢያ መንግሥት የሀገራችንን ዕድገት ለመግታት በተለያዩ ጊዜያት የሚፈፅማቸውን የሽብርተኝነት ተግባሮች መላው ህብረተሰብና አቻ የፓርላማ አባላት እንዲገነዘቡ ሠፊ ሥራ ተሠርቷል፡፡

 የተከበራችሁ የምክር ቤት አባላት!

 ምክር ቤታችን በሦስተኛው የሥራ ዘመን በሁለተኛ ዓመት የሥራ ጊዜው ለምክር ቤቱ የተሰጡትን ሥልጣንና ኃላፊነቶች ለመወጣት ያደረገው ጥረትና የተገኘው ውጤት የሚያበረታታ መሆኑን ተመልክተናል፡፡ በመሆኑም የ5 ዓመቱን ስትራቴጂክ ዕቅዳችንን መሠረት በማድረግ በሚቀጥለው ዓመት በተጠናከረ ሁኔታ የምክር ቤታችንን ተልዕኮ ሊያሳኩ የሚችሉ እና ለዓመቱ ዕቅድ ዝርዝር መነሻ ሊሆኑ የሚችሉ ዋና ዋና ተግባሮች እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡

 በአቅም ግንባታ ዙሪያ ለምክር ቤቱ አባላት፣ ለቋሚ ኮሚቴዎች፣ ለፅ/ቤቱ ባለሙያዎችና ለህገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ አባላት ከምክር ቤቱ ተልዕኮ አንፃር የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና መስጠትና የፌዴራሊዝም ሥርዓት ከሚከተሉት ሀገሮች ጋርም ጠንካራ ግንኙነት በመፍጠር የአቻ ፓርላማ አሠራር ልምድ ልውውጥ ማድረግ፣ በየክልሉ የሚገኙትን ምክር ቤቶች ለማጠናከር በፌዴራሊዝም ሥርዓት ግንባታ፣ በግጭት አፈታት ዙሪያ እና በምክር ቤቶቹ አመራር ዙሪያ ሥልጠና እንዲያገኙ ማድረግ፣

 ከዚህም ሌላ ህገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለማጠናከር የህገ-መንግሥት ግንዛቤ እንዲዳብር ማድረግ፣ ለዚህም በመገናኛ ብዙሃን በተለያዩ ሥልቶች መሠረታዊ የህገ-መንግሥት መርሆዎችን ማስጨበጥ፣ ለአያያዝ በሚያመች መልኩ የህገ-መንግሥት ቅጂዎችን ማሳተምና በከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና በክልሎች በስፋት እንዲሰራጩ ማድረግ፣ በተቻለ መጠን ወደ ተለያዩ ቋንቋዎች መተርጐም፣ የህገ-መንግሥት አርቃቂ ኮሚሽን የውይይት ሂደት ከድምፅ ወደ ፅሑፍ በመለወጥ የህገ-መንግሥት አጣሪ ጉባኤ እና ሌሎች ተቋማት እንዲጠቀሙ ማድረግ፣ ለክልሎች የሚሰጠው የድጐማ በጀትና የጋራ ገቢዎች ክፍፍልም አንዴ ተሠርቶ የሚያበቃ ባለመሆኑ በዓመቱ ትኩረት ከሚሰጣቸው ተግባሮች አንዱ ነው፡፡ በዚህ ዙሪያ ሁለት ሥራዎች የሚሰሩ ይሆናል፡፡ የመጀመሪያው አሁን ተዘጋጅቶ የቀረበውን አዲሱን የድጐማ በጀት ማከፋፈያ ቀመር በምክር ቤቱ ከፀደቀ የውጭውን ተሞክሮ ባገናዘበ አዳዲስ አመልካቾችን በማካተት እና በየጊዜው መረጃዎችን በማጥራት ማሻሻል፣ ሁለተኛው የጋራ ገቢዎች በፌዴራልና በክልሎች መካከል የሚከፋፈሉበትን ቀመር ማዘጋጀትና በምክር ቤቱ ማስወሰን፣

 በዓመታዊ ዕቅዱ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ሌላው ጉዳይ አሁን የተጀመረው ጥናት የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን አንድነትና ማንነት ሊያንፀባርቅና ለመጪው ትውልድ ሊተላለፍ በሚችል መልኩ በጥልቀት ማጠናከር ነው፡፡ ከዚህ ሌላ በተለያዩ ክልሎች ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ልምዳቸውን እንዲለዋወጡና እንዲቀራረቡ የሚያስችሉ ተግባራትን መፈፀም ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም በየጊዜው የተለያዩ መድረኮች ተዘጋጅቶ፣ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ውይይት ይደረጋል፤

 የተከበራችሁ የምክር ቤት አባላት!

 እንደሚታወቀው ሀገራችን አዲሱን ሚሊንየም ለመቀበል ከፍተኛ ዝግጅት በማድረግ ላይ ትገኛለች፡፡ አገራችን የምትታወቀው በድርቅና በኋላቀርነት በመሆኑ አዲሱ ሚሊኒየም የኢትዮጵያን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ማንነትና መልካም ገፅታ ለመላው የሀገራችን ህዝቦችና ለአለም ዓቀፉ ህብረተሰብ የምናስተዋውቅበት ጥሩ አጋጣሚ ነው። ይህንኑ ተግባር ለማጠናከር የፌዴሬሽን ም/ቤት በቅርቡ ከ200 የማያንሱ የመገናኛ ብዙሃን፣ የሥነ-ጥበባትና የቋንቋ ባለሙያዎችን ያካተተ የውይይት መድረክ በማዘጋጀት ግንዛቤ እንዲያገኙ አድርጓል፡፡ በነዚህ አካላት ላይ ትኩረት የተደረገበት ምክንያት ለሙያው ካላቸው ቅርበት አንጻር የብሔሮች፣ብሔረሰቦችንና ህዝቦችን መልካም ገጽታ በማስተዋወቅ ረገድ ከፍተኛ ሚና ሊጫወቱ ስለሚችሉ ነው።  ለዚህ እንቅስቃሴ ስኬታማነት ምክር ቤታችን ከሌሎች አቻ ተቋማት ጋር የጋራ ዕቅድ ያዘጋጀ ሲሆን የተለያዩ ተግባራት እንደሚከናወኑ ግንዛቤ ተወስዷል፡፡ በዚህ ዙሪያ የምክር ቤቱ አባላት ሠፊ ተሳትፎ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡

 ከዚህ ጋር በተያያዘ የህዝቦችን ዲሞክራሲያዊ አንድነት የሚያጠናክሩ፣ መተማመንና ግልፅነትን ለመፍጠር የሚያስችሉ መደበኛ አሠራሮችን መዘርጋት ወሳኝ በመሆኑ፣ ለምክር ቤታችን በህገ-መንግሥቱና በሌሎች ህጐች የተሰጡትን መብቶች በመጠቀም ህገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን የሚያጠናክሩና የተመጣጠነ ዕድገት በህዝቦች መካከል መኖራቸውን ለማረጋገጥና ለማስተካከል የተለያዩ የፌዴራል መሥሪያ ቤቶችና ተቋማት ለምክር ቤታችን እንደአስፈላጊነቱ ማብራሪያ እንዲሰጡ ይደረጋል፡፡

 ለዚህ የተቀደሰ ዓላማ ለመጀመሪያ ጊዜ ከአስፈፃሚው አካል የትምህርት ሚኒስቴር የመጀመሪያው ዕድል ተቋዳሽ በመሆኑ ግንባር ቀደም ሚና በመጫወት ለሌሎች ተቋማት አርአያ እንደሚሆን ተስፋ እናደርጋለን፡፡

  ለሁለተኛ ጊዜ በመላው ሀገራችንና በዋነኛነት ደግሞ ባለብዙ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በሆነው በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል መንግሥት የሚከበረው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል ከምንጊዜም በላይ የህዝቦች ማንነት የሚንፀባረቅበት እና የሚሊንየም በዓላችንን የሚያደምቅ መድረክ እንዲሆን ጥረት እናደርጋለን፡፡ ለዚህም ቅድመ ዝግጅቱ ከፌዴሬሽን ምክር ቤትና ከክልሉ ጋር በቅርበት የሚከናወን ይሆናል፡፡

 በመጨረሻም የሀገራችንን መልካም ገፅታ ለማስተዋወቅ የዲኘሎማሲ ሥራዎቻችን በተጠናከረ ሁኔታ መቀጠል እንዳለባቸው እያሳሰብኩ፣ መጪው የሚሊኒየም በዓል አገራችን ወደ ዕድገት ጐዳና እያመራች መሆኑንና መልካም ገፅታችንን ለአለም ዓቀፍ ህብረተሰብ የምናስረዳበት  አጋጣሚ በመሆኑ በዚህ ዙሪያ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ እንዳለብን ለማስገንዘብ እወዳለሁ፡፡

                                                               አመሰግናለሁ

                                                      ግንቦት 1999