ታሪክ
አወቃቀር
አፈ-ጉባኤዎች
አባላት
የስነምግባር ደንብ
ሥልጣንና ተግባር
ህጋዊ መሠረቶች
ህግ መንግስት
ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 251/1993
የስብሰባና የስነስራት ደንብ
ሌሎች
ቋሚ ኮሚቴዎች
አባላት
የስነምግባር ደንብ
ውሳኔ ያገኙ ጉዳዮች 
ህገመንግስታዊ ትርጉም 
የህገመንግስትና የክልል ጉዳዮች
የገቢዮችና ድጎማ ጉዳዮች
ሌሎች
በሂደት ላይ ያሉ ጉዳዮች
ስትራቴግክ እቅድ
ቃለ-ጉባኤ
ሪፖርት
ህትመቶች
ፎርሞች
ዜና
ጨረታ
ማስታወቂያ
መልስ
የፎቶ ማህደር
ጠቃሚ አድራሻዎች
 
 
ሕገ መንግስት
     

የኦሮምኛ ህገ መንግስት


የትግርኛ ህገ መንግስት

   
 
 
     

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ

ሪፐብሊክ

ሕገ መንግሥት

ምዕራፍ አንድ - ጠቅላላ ድንጋጌዎች

ምዕራፍ ሁለት - የሕገ መንግሥቱ መሰረታዊ መርሆዎች

ምዕራፍ ሦስት - መሰረታዊ መብቶች

ምዕራፍ አራት - የመንግሥት አወቃቀር

ምዕራፍ አምስት - የሥልጣን አወቃቀር እና ክፍፍል

ምዕራፍ ስድስት - ስለፌዴራሉ መንግሥት ምክር ቤቶች

ምዕራፍ ሰባት - ስለ ሪፐብሊኩ ኘሬዚዳንት

ምዕራፍ ስምንት - የሕግ አስፈጻሚ አካል

ምዕራፍ ዘጠኝ - ስለ ፍርድ ቤቶች አወቃቀርና ሥልጣን

ምዕራፍ አስር - የብሔራዊ ፖሊሲ መርሆዎችና ዓላማዎች

ምዕራፍ አሥራ አንድ - ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች

መ ግ ቢ ያ

እኛ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች፡በሀገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ ዘላቂ ሰላም፣ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እንዲሰፍን፣ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እድገታችን እንዲፋጠን፣ የራሳችንን ዕድል በራሳችን የመወሰን መብታችንን ተጠቅመን፣ በነጻ ፍላጐታችን፣ በሕግ የበላይነት እና በራሳችን ፈቃድ ላይ የተመሰረተ አንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብ በጋራ ለመገንባት ቆርጠን በመነሳት፤ይህን ዓላማ ከግብ ለማድረስ፣ የግለሰብና የብሔር/ብሔረሰብ መሰረታዊ መብቶች መከበራቸው፣ የጾታ እኩልነት መረጋገጡ፣ ባሕሎችና ሃይማኖቶች ካለአንዳች ልዩነት እንዲራመዱ የማድረጉ አስፈላጊነት ጽኑ እምነታችን በመሆኑ፤ኢትዮጵያ ሀገራችን የየራሳችን አኩሪ ባሕል ያለን፣ የየራሳችን መልክዓ ምድር አሰፋፈር የነበረንና ያለን፣ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በተለያዩ መስኮችና የግንኙነት ደረጃዎችተሳስረንአብረን የኖርንባትና የምንኖርባት ሀገር በመሆንዋ፤ ያፈራነው የጋራ ጥቅምና አመለካከት አለን ብለን ስለምናምን፤መጪው የጋራ ዕድላችን መመስረት ያለበት ከታሪካችን የወረስነውን የተዛባ ግንኙነት በማረምና የጋራ ጥቅማችንን በማሳደግ ላይ መሆኑን በመቀበል፤ ጥቅማችንን፣ መብታችንና ነጻነታችንን በጋራ እና በተደጋጋፊነት ለማሳደግ አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ የመገንባቱን አስፈላጊነት በማመን፤ በትግላችንና በከፈልነው መስዋዕትነት የተገኘውን ዴሞክራሲና ሰላም ዘላቂነቱንለማረጋገጥ፤ይህ ሕገ መንግሥት ከዚህ በላይ ለገለጽናቸው ዓላማዎችና እምነቶች ማሰሪያ እንዲሆነንእንዲወክሉን መርጠን በላክናቸው ተወካዮቻቸን አማካይነት በሕገ መንግሥት ጉባኤ ዛሬ ኅዳር 29 ቀን 1987 አጽድቀነዋል፡፡

ምዕራፍ አንድ

ጠቅላላ ድንጋጌዎች

አንቀጽ 1

የኢትዮጵያ መንግሥት ስያሜ

ይህ ሕገ መንግሥት ፌዴራላዊና ዴሞክራሲያዊ የመንግሥት አወቃቀር ይደነግጋል፡፡በዚህ መሰረት የኢትዮጵያ መንግሥት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ በሚል ስም ይጠራል፡፡

አንቀጽ 2

የኢትዮጵያ የግዛት ወሰን

የኢትዮጵያ የግዛት ወሰን የፌዴራሉን አባሎች ወሰን የሚያጠቃልል ሆኖ በዓለም አቀፍ

ስምምነቶች መሰረት የተወሰነው ነው፡፡

አንቀጽ 3

የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ

1. የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከላይ አረንጓዴ፣ ከመሐል ቢጫ፣ ከታች ቀይ ሆኖበመሐሉ ብሔራዊ ዓርማ ይኖረዋል፡፡   ሦስቱም ቀለማት እኩል ሆነው በአግድም ይቀመጣሉ፡፡

2. ከሰንደቅ ዓላማው ላይ የሚቀመጠው ብሔራዊ ዓርማ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣

ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች እና ሃይማኖቶች በእኩልነትና በአንድነት ለመኖር ያላቸውን

ተስፋ የሚያንጸባርቅ ይሆናል፡፡

3. የፌዴራሉ አባሎች የየራሳቸው ሰንደቅ ዓላማና ዓርማ ሊኖራቸው ይችላል፡፡

ዝርዝሩን በየራሳቸው ምክር ቤት ይወስናሉ፡፡

አንቀጽ 4

የኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙር

የኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙር የሕገ መንግሥቱን ዓላማዎችና የኢትዮጵያ ሕዝቦች በዴሞክራሲ ሥርዓት አብረው ለመኖር ያላቸውን እምነት፣ እንዲሁም የወደፊት የጋራ ዕድላቸውን የሚያንጸባርቅ ሆኖ በሕግ ይወሰናል፡፡

አንቀጽ 5

ስለ ቋንቋ

1. ማናቸውም የኢትዮጵያ ቋንቋዎች በእኩልነት የመንግሥት እውቅና ይኖራቸዋል፡፡

2. አማርኛ የፌዴራሉ መንግሥት የሥራ ቋንቋ ይሆናል፡፡

3. የፌዴሬሽኑ አባሎች የየራሳቸውን የሥራ ቋንቋ በሕግ ይወስናሉ፡፡

አንቀጽ 6

ስለ ዜግነት

1. ወላጆቹ/ወላጆኟ ወይም ከወላጆቹ/ከወላጆኟ አንደኛቸው ኢትዮጵያዊ/ኢትዮጵያዊት የሆነ/የሆነች የኢትዮጵያ ዜጋ ነው/ናት፡፡

2. የውጭ ሀገር ዜጐች የኢትዮጵያ ዜግነት ሊያገኙ ይችላሉ፡፡

3. ዜግነትን በሚመለከት ዝርዝሩ በሕግ ይወሰናል፡፡

አንቀጽ 7

የፆታ አገላለጽ

በዚህ ሕገ መንግሥት ውስጥ በወንድ ፆታ የተደነገገው የሴትንም ፆታ ያካትታል፡፡

ምዕራፍ ሁለት

የሕገ መንግሥቱ መሰረታዊ መርሆዎች

አንቀጽ 8

የሕዝብ ሉዓላዊነት

1. የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሥልጣንባለቤቶች ናቸው፡፡

2. ይህ ሕገ መንግሥት የሉዓላዊነታቸው መግለጫ ነው፡፡

3. ሉዓላዊነታቸውም የሚገለጸው በዚህ ሕገ መንግሥት መሰረት በሚመርጧቸው ተወካዮቻቸውና በቀጥታ በሚያደርጉት ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ አማካይነት ይሆናል፡፡

አንቀጽ 9

የሕገ መንግሥት የበላይነት

1. ሕገ መንግሥቱ የሀገሪቱ የበላይ ሕግ ነው፡፡ ማንኛውም ሕግ፣ ልማዳዊ አሰራር፣

እንዲሁም የመንግሥት አካል ወይም ባለሥልጣን ውሳኔ ከዚህ ሕገ መንግሥት

ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈጻሚነት አይኖረውም፡፡

2. ማንኛውም ዜጋ፣ የመንግሥት አካላት፣ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ሌሎች ማኅበራት

እንዲሁም ባለሥልጣኖቻቸው፣ ሕገ መንግሥቱን የማስከበርና ለሕገ መንግሥቱ

ተገዢ የመሆን ኃላፊነት አለባቸው፡፡

3. በዚህ ሕገ መንግሥት ከተደነገገው ውጭ በማናቸውም አኳኊን የመንግሥት

ሥልጣን መያዝ የተከለከለ ነው፡፡

4. ኢትዮጵያ ያጸደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የሀገሪቱ ሕግ አካል ናቸው፡፡

አንቀጽ 10

የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች

1. ሰብዓዊ መብቶችና ነጻነቶች ከሰው ልጅ ተፈጥሮ የሚመነጩ፣ የማይጣሱና የማይገፈፉ ናቸው፡፡

2. የዜጐች እና የሕዝቦች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ይከበራሉ፡፡

አንቀጽ 11

የመንግሥትና የሃይማኖት መለያየት

1. መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው፡፡

2. መንግሥታዊ ሃይማኖት አይኖርም፡፡

3. መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም፡፡ ሃይማኖትም በመንግሥት ጉዳይ

ጣልቃ አይገባም፡፡

አንቀጽ 12

የመንግሥት አሠራርና ተጠያቂነት

1. የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ግልጽ በሆነ መንገድ መከናወን አለበት፡፡

2. ማንኛውም ኃላፊና የሕዝብ ተመራጭ ኃላፊነቱን ሲያጓድል ተጠያቂ ይሆናል፡፡

ሕዝብ በመረጠው ተወካይ ላይ እምነት ባጣ ጊዜ ከቦታው ለማንሳት ይችላል፡፡

ዝርዝሩ በሕግ ይወሰናል፡፡

ምዕራፍ ሦስት

መሰረታዊ መብቶችና ነጻነቶች

አንቀጽ 13

ተፈጻሚነትና አተረጓጐም

1. በማንኛውም ደረጃ የሚገኙ የፌዴራል መንግሥትና የክልል ሕግ አውጪ፣ ሕግ አስፈጻሚ እና የዳኝነት አካሎች በዚህ ምዕራፍ የተካተቱን ድንጋጌዎች የማክበርና የማስከበር ኃላፊነትና ግዴታ አለባቸው፡፡

2. በዚህ ምዕራፍ የተዘረዘሩት መሠረታዊ የመብቶችና የነጻነቶች ድንጋጌዎች ኢትዮጵያ ከተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ሕግጋት፣ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ስምምነቶችና ዓለም አቀፍ ሰነዶች መርሆዎች ጋር በተጣጣመ መንገድ

ይተረጐማል፡፡

ክፍል አንድ

ሰብዓዊ መብቶች

አንቀጽ 14

የሕይወት፣ የአካል ደህንነትና የነጻነት መብት

ማንኛውም ሰው ሰብዓዊ በመሆኑ የማይደፈርና የማይገሰስ በሕይወት የመኖር፣ የአካል

ደህንነትና የነጻነት መብት አለው፡፡

አንቀጽ 15

የሕይወት መብት

ማንኛውም ሰው በሕይወት የመኖር መብት አለው፡፡ ማንኛውም ሰው በሕግ በተደነገገ

ከባድ የወንጀል ቅጣት ካልሆነ በስተቀር ሕይወቱን አያጣም፡፡

አንቀጽ 16

የአካል ደህንነት መብት

ማንኛውም ሰው በአካሉ ላይ ጉዳት እንዳይደርስበት የመጠበቅ መብት አለው፡፡

አንቀጽ 17

የነጻነት መብት

1. በሕግ ከተደነገገው ሥርዓት ውጭ ማንኛውም ሰው ወንድም ሆነ ሴት ነጻነቱን/ቷን

አያጣም/አታጣም፡፡

2. ማንኛውም ሰው በሕግ ከተደነገገው ሥርዓት ውጭ ሊያዝ፣ ክስ ሳይቀርብበት

ወይም ሳይፈረድበት ሊታሰር አይችልም፡፡

አንቀጽ 18

ኢሰብዓዊ አያያዝ ስለመከልከሉ

1. ማንኛውም ሰው ጭካኔ ከተሞላበት፣ ኢሰብዓዊ ከሆነ ወይም ክብሩን ከሚያዋርድ አያያዝ ወይም ቅጣት የመጠበቅ መብት አለው፡፡

2. ማንኛውም ሰው በባርነት ወይም በግዴታ አገልጋይነት ሊያዝ አይችልም፡፡ለማንኛውም ዓላማ በሰው የመነገድ ተግባር የተከለከለ ነው፡፡

3. ማንኛውም ሰው በኃይል ተገዶ ወይም ግዴታ ለማሟላት ማንኛውንም ሥራ እንዲሠራ ማድረግ የተከለከለ ነው፡፡

4. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 3 «በኃይል ተገዶ ወይም ግዴታን ለማሟላት»የሚለው ሐረግ የሚከተሉትን ሁኔታዎች አያካትትም፤

ሀ/ ማንኛውም እስረኛ በእስራት ላይ ባለበት ጊዜ በሕግ መሠረት አንዲሠራ የተወሰነውን ወይም በገደብ ከእስር በተለቀቀበት ጊዜ፣ የሚሠራውን ማንኛውም ሥራ፣

ለ/ ማንኛውም ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ሕሊናው የማይፈቅድለት ሰው በምትክ የሚሰጠውን አገልግሎት፣

ሐ/ የማኅበረሰቡን ሕይወት ወይም ደህንነት የሚያሰጋ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ወይም አደጋ በሚያጋጥምበት ጊዜ የሚሰጥ ማንኛውም አገልግሎት፣

መ/ በሚመለከተው ሕዝብ ፈቃድ በአካባቢው የሚፈጸመውን ማንኛውንም ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ የልማት ሥራ፡፡

አንቀጽ 19

የተያዙ ሰዎች መብት

1. ወንጀል ፈጽመዋል በመባል የተያዙ ሰዎች የቀረበባቸው ክስና ምክንያቶቹ በዝርዝር ወዲያውኑ በሚገባቸው ቋንቋ እንዲነገራቸው መብት አላቸው፡፡

2. የተያዙ ሰዎች ላለመናገር መብት አላቸው፤ የሚሰጡት ማንኛውም ቃል ፍርድ ቤት በማስረጃነት ሊቀርብባቸው እንደሚችል መረዳት በሚችሉት ቋንቋ እንደተያዙ ወዲያውኑ ማስገንዘቢያ እንዲሰጣቸው መብት አላቸው፡፡

3. የተያዙ ሰዎች በአርባ ስምንት ሰዓታት ውስጥ ፍርድ ቤት የመቅረብ መብት አላቸው፡፡ ይህም ጊዜ ሰዎቹ ከተያዙበት ቦታ ወደ ፍርድ ቤት ለመምጣት አግባብ ባለው ግምት የሚጠይቀውን ጊዜ አይጨምርም፡፡ ወዲያውኑ ፍርድ ቤት እንደቀረቡ በተጠረጠሩበት ወንጀል ለመታሰር የሚያበቃ ምክንያት ያለ መሆኑ ተለይቶ አንዲገለጽላቸው መብት አላቸው፡፡

4. የያዛቸው የፖሊስ መኮንን ወይም የሕግ አስከባሪ በጊዜው ገደብ ፍርድ ቤት በማቅረብ የተያዙበትን ምክንያት ካላስረዳ፣ ፍርድ ቤቱ የአካል ነጻነታቸውን እንዲያስከብርላቸው የመጠየቅ ሊጣስ የማይችል መብት አላቸው፡፡ ሆኖም ፍትሕ

እንዳይጓደል ሁኔታው የሚጠይቅ ከሆነ ፍርድ ቤቱ የተያዘው ሰው በጥበቃ ሥር እንዲቆይ ለማዘዝ ወይም ምርመራ ለማካሄድ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ሲጠየቅ አስፈላጊ በሆነ መጠን ብቻ ሊፈቅድ ይችላል፡፡ የሚያስፈልገውን ተጨማሪ ጊዜ

ፍርድ ቤቱ ሲወስን ኃላፊ የሆኑት የሕግ አስከባሪ ባለሥልጣኖች ምርመራውን አጣርተው የተያዘው ሰው በተቻለ ፍጥነት ፍርድ ቤት እንዲቀርብ ያለውን መብት የሚያስከብር መሆን አለበት፡፡

5. የተያዙ ሰዎች በራሳቸው ላይ በማስረጃነት ሊቀርብ የሚችል የእምነት ቃል እንዲሰጡ ወይም ማናቸውንም ማስረጃ እንዲያምኑ አይገደዱም፡፡ በማስገደድ የተገኘ ማስረጃ ተቀባይነት አይኖረውም፡፡

6. የተያዙ ሰዎች በዋስ የመፈታት መብት አላቸው፡፡ ሆኖም በሕግ በተደነገጉ ልዩ ሁኔታዎች ፍርድ ቤት ዋስትና ላለመቀበል ወይም በገደብ መፍታትን ጨምሮ በቂ የሆነ የዋስትና ማረጋገጫ እንዲቀርብ ለማዘዝ ይችላል፡፡

አንቀጽ 20

የተከሰሱ ሰዎች መብት

1. የተከሰሱ ሰዎች ክስ ከቀረበባቸው በኃላ ተገቢ በሆነ አጭር ጊዜ ውስጥ በመደበኛ ፍርድ ቤት ለሕዝብ ግልጽ በሆነ ችሎት የመሰማት መብት አላቸው፡፡ ሆኖም የተከራካሪዎቹን የግል ሕይወት፣ የሕዝብን የሞራል ሁኔታና የሀገሪቱን ደህንነት

ለመጠበቅ ሲባል ብቻ ክርክሩ በዝግ ችሎት ሊሰማ ይችላል፡፡

2. ክሱ በቂ በሆነ ዝርዝር እንዲነገራቸው እና ክሱን በጽሁፍ የማግኘት መብት አላቸው፡፡

3. በፍርድ ሂደት ባሉበት ጊዜ በተከሰሱበት ወንጀል እንደ ጥፋተኛ ያለመቆጠር፣በምስክርነት እንዲቀርቡም ያለመገደድ መብት አላቸው፡፡

4. የቀረበባቸውን ማናቸውንም ማስረጃ የመመልከት፣ የቀረቡባቸውን ምስክሮች የመጠየቅ፣ ለመከላከል የሚያስችላቸውን ማስረጃ የማቅረብ ወይም የማስቀረብ እንዲሁም ምስክሮቻቸው ቀርበው እንዲሰሙላቸው የመጠየቅ መብት አላቸው፡፡

5. በመረጡት የሕግ ጠበቃ የመወከል ወይም ጠበቃ ለማቆም አቅም በማጣታቸው ፍትሕ ሊጓደል የሚችልበት ሁኔታ ሲያጋጥም ከመንግሥት ጠበቃ የማግኘት መብት አላቸው፡፡

6. ክርክሩ በሚታይበት ፍርድ ቤት በተሰጠባቸው ትእዛዝ ወይም ፍርድ ላይ ሥልጣን ላለው ፍርድ ቤት ይግባኝ የማቅረብ መብት አላቸው፡፡

7. የፍርዱ ሂደት በማይገባቸው ቋንቋ በሚካሄድበት ሁኔታ በመንግሥት ወጪ ክርክሩ እንዲተረጐምላቸው የመጠየቅ መብት አላቸው፡፡

አንቀጽ 21

በጥበቃ ሥር ያሉና በፍርድ የታሰሩ ሰዎች መብት

1. በጥበቃ ሥር ያሉና በፍርድ የታሰሩ ሰዎች ሰብዓዊ ክብራቸውን በሚጠብቁ

ሁኔታዎች የመያዝ መብት አላቸው፡፡

2. ከትዳር ጓደኞቻቸው፣ ከቅርብ ዘመዶቻቸው፣ ከጓደኞቻቸው፣ ከሃይማኖት

አማካሪዎቻቸው፣ ከሐኪሞቻቸው እና ከሕግ አማካሪዎቸው ጋር ለመገናኘትና

እንዲጐበቿቸውም ዕድል የማግኘት መብት አላቸው፡፡

አንቀጽ 22

የወንጀል ሕግ ወደኊላ ተመልሶ የማይሰራ ስለመሆኑ

1. ማንኛውም ሰው የወንጀል ክስ ሲቀርብበት የተከሰሰበት ድርጊት በተፈጸመበት ጊዜ ድርጊቱን መፈጸሙ ወይም አለመፈጸሙ ወንጀል መሆኑ በሕግ የተደነገገ ካልሆነ በስተቀር ሊቀጣ አይችልም፡፡ እንዲሁም ወንጀሉን በፈጸመበት ጊዜ

ለወንጀሉ ተፈጻሚ ከነበረው የቅጣት ጣሪያ በላይ የከበደ ቅጣት በማንኛውም ሰው ላይ አይወሰንም፡፡

2. የዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 ቢኖርም፣ ድርጊቱ ከተፈጸመ በኊላ የወጣ ሕግ ለተከሳሹ ወይም ለተቀጣው ሰው ጠቃሚ ሆኖ ከተገኘ ከድርጊቱ በኊላ የወጣው ሕግ ተፈጻሚነት ይኖረዋል፡፡

አንቀጽ 23

በአንድ ወንጀል ድጋሚ ቅጣት ስለመከልከሉ

ማንኛውም ሰው በወንጀል ሕግና ሥነ ሥርዓት መሠረት ተከሶ የመጨረሻ በሆነ ውሳኔ

ጥፋተኛነቱ በተረጋገጠበት ወይም በነጻ በተለቀቀበት ወንጀል እንደገና አይከሰስም ወይም

አይቀጣም፡፡

አንቀጽ 24

የክብርና የመልካም ስም መብት

1. ማንኛውም ሰው ሰብዓዊ ክብሩና መልካም ስሙ የመከበር መብት አለው፡፡

2. ማንኛውም ሰው የራሱን ስብዕና ከሌሎች ዜጐች መብቶች ጋር በተጣጣመ ሁኔታ በነጻ የማሳደግ መብት አለው፡፡

3. ማንኛውም ሰው በማንኛውም ስፍራ በሰብዓዊነቱ እውቅና የማግኘት መብት አለው፡፡

አንቀጽ 25

የእኩልነት መብት

ሁሉም ሰዎች በሕግ ፊት እኩል ናቸው፤ በመካከላቸውም ማንኛውም ዓይነት ልዩነት ሳይደረግ በሕግ እኩል ጥበቃ ይደረግላቸዋል፡፡ በዚህ ረገድ በዘር፣በብሔር፣ ብሔረሰብ፣በቀለም፣ በጾታ፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ፣ በማኅበራዊ አመጣጥ፣ በሀብት፣በትውልድ ወይም በሌላ አቋም ምክንያት ልዩነት ሳይደረግ ሰዎች ሁሉ እኩልና ተጨባጭ

የሕግ ዋስትና የማግኘት መብት አላቸው፡፡