|
ም/ቤቱ የፌዴራል መንግስት አባል ክልሎች የሚገኙ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ተወካይ የሆኑ 108 አባላት ባካሄዱበት ስብሰባ የተግባር እንቅስቃሴውን ጀምሯል፡፡ የየክልሉ የብሔር ብሔረሰብና ህዝብ ውክልና ሲታይ ህገ-መንግስቱን መሠረት ያደረገና 58 ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች የተወከሉበት ነበር፡፡
በወቅቱ የነበረው የም/ቤቱ አባላት አመራረጥ በህገ-መንግስቱ አንቀፅ 61/3 መሠረት በየክልሉ ም/ቤቶች የተከናወነ እና የተወካዮች ብዛትም በአንቀፅ 61/2 መሠረት እያንዳንዱ ብሔር ብሔረሰብ ሕዝብ በብሔርነቱ ወይም በብሔረሰብነቱ አንድ ተወካይ እና በተጨማሪ የብሔር ወይም የብሔረሰቡ አንድ ሚሊዮን ሕዝብ አንድ ተጨማሪ ወኪል በፌዴሬሸን ም/ቤት ውስጥ ሊኖረው እንደሚችል ተደንግጓል፡፡
በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፕብሊክ ሕገ-መንግስት የፌዴሬሸን ም/ቤት በአንድ በኩል የአገራችን ብሔር ብሔረሰብና ሕዝቦች የተቀዳጇቸው መብቶች ሳይሸራረፉ በተግባር እንዲተረጎሙ፤ በሌላ በኩል ደግሞ በህዝቦች መካከል ያለው አንድነት በእኩልነትና በፅኑ መሠረት ላይ እንዲገነባ ለማድረግ ከፍተኛ ኃላፊነት የተሸከመ ም/ቤት ነው፡፡
ለፌዴሬሸን ም/ቤት መመስረት አንደዋነኛ ምክንያት የሚጠቀሰው ጉዳይ የኢፌዴሪ ሕገ-መንግስት የራስን እድል በራስ የመወሰን እስከመገንጠል መብትን የተቀበለ እና፣ ህገ-መንግስቱ በህዝቦች ስምምነት ላይ የተመሠረተ ስለሆነ የሕዝቦችን አንድነት ለማስጠበቅና ልዩነቶችም ከተከሰቱ በህገ-መንግስቱ መሠረት መፍትሔ በመስጠት ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ስር መስደድ የበኩሉን ሚና እንዲጫወት ለማድረግ ነው፡፡
የፌዴሬሽን ምክር ቤት የመጀመሪያ ስብሰባው የተከፈተው በኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ሊቀመንበር በክቡር አቶ ከማል በድሪ ሲሆን በወቅቱ በምክር ቤቱ አሰራርና የስብሰባ ስነ ስርዓት ደንብ የዋና አፈጉባኤ አመራረጥ አንቀፅ 51 መሠረት ከተጠቆሙት ሁለት እጩዎች ወ/ሮ አልማዝ መኮ ከኦሮምያ ክልል በዋና አፈጉባኤነት፣ በተመሳሳይ ሁኔታ ለምክትል አፈ ጉባኤነት ከተጠቆሙት ሁለት አጩዎች አቶ ዚያድ በድሪ ከሶማሌ ክልል ሲመረጡ ምክትል አፈ-ጉባኤውን ክልሉ ስለሳባቸው (ሰለፈለጋቸው) ምክር ቤቱ ሚያዝያ 3/1989 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባ በምትካቸው የተከበሩ ዶ/ር መሀመድ ሰርሐዬን በመምረጥ ተተክተው እንዲሰሩ ተደርጓል እንዲሁም ም/ቤቱ በመስከረም 28/1995 ዓ.ም. መደበኛ ስብሰባው በወ/ሮ አልማዝ መኮ ምትክ ክቡር ዶ/ር ሙላቱ ተሾመን በዋና አፈ-ጉባኤነት መርጧል፡፡ ምክርቤቱ የተጣለበትን ሃላፊነቶች ለመወጣት ያስችለው ዘንድ፤ ከመስከረም 1993ዓ.ም. ጀምሮ ሦስት ኮሚቴዎችን አቋቁሞ ሲሰራ ቆይቷል እያንዳንዳቸው አስራአንድ አስራአንድ አባላት የነበሩአቸውን እነዚህ ኮሚቴዎች (1ኛ) የህግ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ (2ኛ) የገቢዎች ድልድል ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ (3ኛ) የክልል ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴን አደረጃጀቶች እንደገና በማየት መስከረም 26-27/1996
ዓ.ም. እያንዳንዳቸው አስራአምስት አስራአምስት አባላት ባላቸው ሁለት ኮሚቴዎች (1ኛ) የበጀት ድጐማና የገቢዎች ክፍፍል ቋሚ ኮሚቴ (2ኛ) የህገ-መንግስት የክልል ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሚል በሁለት እንዲጠቃለሉ ተደርጓል፡፡
ከዚህ ሌላ በህገ-መንግስቱ አንቀፅ 82 መሠረት አስራአንድ አባላት ያሉት የህገ-መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ በማደራጀት ህገ-መንግስታዊ ጉዳዮችን የማጣራትና በፌዴራሉና በክልል ህግ አውጪ አካላት የሚወጡ ህጐች ከህገ-መንግስቱ ጋር ይቃረናሉ የሚል ጥያቄ ሲነሳ ጉዳዩን በመመርመር ሕገ-መንግስታዊ ትርጉም በመስጠት የፌዴሬሽን ምክር ቤት የመጨረሻው ውሳኔ እንዲሰጥበት በማድረግ ሰፊ ተግባራት ተከናውናዋል፡፡ በእስካሁን የምክርቤቱ ቆይታ ከፍተኛ ተግባራት የተከናወኑ ሲሆን በህገ-መንግስቱ መሠረት በአወካከሉ የተወሰኑ |