የፌዴሬሽን ምክር ቤት አገረዊ ኮንፍረንስ
ለሁለት ቀናት አካሄደ
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ለአባላቱ ስለ ግጭት መከላከያና አፈታት ዘዴ የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠና ለሁለት ቀናት ሀምሌ 13 እና 14 1998 ዓ.ም. ሰጠ፡፡
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ዶክተር መሐመድ ሰርሃዬና በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ዶክተር ክላስ ዲክኖፕ በጋራ ስልጠናው ከመሰጠቱ አንድ ቀን ቀደም ብለው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የሥልጠናው ዓላማ የምክር ቤቱን አባላት የግጭት አፈታት ብቃት ለማጎልበትና ሌሎች አገሮች ስለሚከተሏቸው የግጭት አፈታት ተሞክሮዎች ልምድ ለመቅሰም መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ሥልጠናው በክልሎች አካባቢ ግጭቶች ቢከሰቱ ሊፈቱ የሚችሉት በፌዴሬሽን በምክር ቤት ሕገ መንግሥቱን መሰረት ባደረገ ሁኔታ ስለሆነ አዲስ የተመረጡ የምክር ቤቱ አባላት በአግባቡ ስለ ህጉና ግጭት አፈታት ስልቱ ግንዛቤ ለማግኘት እንደሚረዳቸው ገልጸዋል፡፡
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ ደግፌ ቡላ በፌዴራላዊ ሥርዓት ውስጥ የግጭት መከላከልና አፈታት ስልት በሚል ርዕስ ስልጠናው በአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን አዳራሽ ኮንፈረንሱን ሲከፍቱ እንደተናገሩት በብሔር፤ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መካከል ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ለማምጣት፤ መልካም አስተዳደር ለማስፈንና የድህነት ቅነሳ እስትራቴጃችንን ተግባራዊ ለማድረግ ፌዴራላዊ ሥርዓት የጎላ ጠቀሜታ አለው ብለዋል፡፡
የፌዴራል ሥርዓት ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ግጭቶችን ለመፍታት ተመራጭ የመንግስት አወቃቀር መሆኑን አመልክተው፤ በአገሪቱ ከተከሰቱ አነስተኛ ግጭቶች መካከም አብዛኛቹ በክልል ምክር ቤቶች ደረጃ መፍትሄ ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡
የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሀግ መንግሥቱ በተሰጠው ስልጣንና ኀላፊነት መሰረት በክልሎች አለመግባባቶች ሲፈጠሩ በውይይት ለመፍታት ጥረት ማድረጉንና ኀላፊነቱን በብቃት መወጣቱን ገልጸዋል፡፡
ለአንድ ቀን ተኩል በሚካሄደው በዚሁ ኮንፈረንስ ከውጭና ከአገር ውስጥ የመጡ ተሳታፊ ምሁራን በሚያቀርቡት ጥናታዊ ፁሁፎች ከፍተኛ ልምድና ተሞክሮ መቅሰም እንደሚቻል እምነታቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ የስዊዘርላንድ አምባሳደር ረኔ ሻቲ ባደረጉት ንግግር የፌዴራዝም ሥርዓት ሰላምን ለማምጣትና የብሄር ብሄረሰቦች ባህልና ዕምነት የሚያረጋግጥ ብቸኛ መንገድ መሆኑን አመልክተው የፌዴራል ሥርዓት የተለያዩ የፖለቲካ ፖርቲዎች ሐሳባቸውን በሰላማዊ መንገድ እንዲያቀረቡ ሰፊ ዕድል የሚሰጥም አመልክተዋል፡፡
በኢትዮጵያ የተካሄደው ምርጫ በፌዴሬሽን ምክር ቤት አሠራር መሰረት ላይ ለውጥ እንደሚያመጣ ጠቅሰው የዚህ ኮንፈረንስ ዓላማ የሌሎች የፌዴራል አገሮች ዓለም አቀፋዊ ተሞክሮዎች ለማቅረብ፣ግጭቶችን ከመከላከልና ከማረጋጋት አኳያ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት ሥልጠንና ኋላፊነት ምን እንደሚመስል ለማስገንዘብ እንደሆነም አስደተዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ምሁር ረዳት ኘሮፌስር መሐመድ ሐቢብ በግጭት መከላከልና አፈታት ዙርያ በኢፌዴሪ ህገ መንግስቱት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ስልጣንና ተግባር፣በዶክተር ያሽ ፓል ጋይ ኬኒያ፣ በዶ/ር ዲያተር ስሺዘር ሲውዘርላንድ ፣በዶ/ር ፔትራ ስቲንሃርት የጀርመንን እንዲሁም በዶ/ር አክህተር ማጅድ የህንድ ባላችው ልምድ ላይ ጥናታዊ ጽሁፎች ያቀረቡ ሲሆን ከተሳታፊዎቹ ጥያቄዎችና አስተያየቶችም ተነስተው ምላሽ ተሰጥቷል፡፡
ስልጠናው ሲጠናቀቅ የመዝጊያ ንግግር ያደረጉትየፌዴሬሽን ምክር ቤት ም/አፈ-ጉባኤ ዶ/ር መሀመድ ሰርሃዬ በበኩላቸው ይህንን መሰል ስልጠና በአንድ ወቅት ስራ ሳይሆኑ በተከታታይነት መሰጠት እንዳለበትና ይህንም ለማድረግ ምክር ቤቱ ባወጣው የአምስት ዓመት የስትራቴጅክ ፕላን አቅዶ በመንቀሳቀስ ላይ መሆኑን ጠቅሰው እቅዱን ተግባራዊ ለማድረግም የልማት አጋሮች ሚና የላቀ መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡
ለሁለት ቀናት በቆየው የአቅም ግንባታ ሥልጠና ላይ 112 የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት ጨምሮ ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ የክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤዎች ምክትል አፈ ጉባኤዎች፣ የጸጥታና የአስተዳደር ቢሮ ኋላፊዎች፣ የተቃዋሚ ፖርቲ አባላት ተወካዮች፣ ከፌዴራል ጉዳዮችና ከሴቶች ጉዳይ ሚኒስቴሮች፣ ከእንባ ጠባቂ ተቋም፣ ከተወካዮች ምክር ቤት፣ከሰብዓዊ መብትና ከሌሎችም ተቋማት የተወጣጡ 180 ሰዎች ተሳታፊዎች ስልጠናውን ተከፍለዋል፡፡
ሥልጠናው የተዘጋጀው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ከጀርመን የቴክኒክ ተራድኦ ድርጅት፣ ከአሜሪካ የዕርዳታ ድርጅት፣ ከካናዳ ዓለም አቀፍ የዕርዳታ ድርጅትና ከስዊዘርላንድ ኤምባሲ በመተባበር ነው፡፡