የፌዴሬሽን ምክር ቤት የድጋፍ
በጀት ቀመርን አፀደቀ
·
የራሱን የበጀት ድልድል ቀመር የሚመለከት ክፍል እንዲቋቋምም ተወሰነ
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ትናንት ባካሄደው ሦስተኛ የፓርላማ ዘመን አንደኛ ዓመት የሥራ ዘመን የመጀመሪያው አስቸኳይ ስብሰባ የ1999ን የበጀት ዓመት ቀመር አጸደቀ፡፡
ምክር ቤቱ የበጀት የድጐማና የገቢዎች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረበው የውሳኔ ረቂቅ ሀሳብ ላይ ከተወያየ በኋላ በ1998 የበጀት ዓመት ጥቅም ላይ የዋለው የበጀት ቀመረ ለ1999 በጀት ዓመትም እንዲያገለግል በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
የኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ አያሌው ጎበዜ በውይይቱ ወቅት እንደገለጹት በአዲሱ የድጋፍ በጀት ማከፋፈያ ቀመር ይዘት ላይ በመርህ ደረጃ ከመግባባት ላይ የተደረሰ ቢሆንም ቴክኒካዊ በሆኑ ሂደቶች ላይ የሚታዩ ጉድለቶች እንዲሁም ካለበት ጥልቅ ባህርይ አንፃር የጋራ ግንዛቤ መጨበጥና ሁሉንም ሊያግባባ በሚችል ደረጃ ሊደርስ ባለመቻሉ ኮሚቴው አዲሱን ቀመረ ተቀብሎ ለምክር ቤቱ የውሳኔ ሀሳብ ሊያቀርብ አላስቻለውም፡፡
በዚህ መሰረትም በቂ ጊዜ ተወስዶና ሠፊና በቂ ጥናት ተካሂዶበት ሁሉንም ወገኖች ሊያግባባ በሚችልና መርሆቹን ለመፈጸም በሚያስችል መልኩ ተዘጋጅቶ እስኪቀርብ በ1998 ዓ.ም. ጥቅም ላይ በዋለው ቀመር አማካይነት ማለትም በ1995 የበጀት ዓመት ለክልሎች የተሰጣቸውን የመደበኛ በጀት ፍላጐት መጠን በተመሳሳይ ለ1999 ከተሰጣቸው በኋላ ቀሪው የሕዝብ ብዛት 65 በመቶ፣ የልማት ደረጃ ልዩነት ወጪ ፍላጎት 25
በመቶ፣ የገቢ መሰብሰብ ጥረትና የሴክተር አፈፃፀም 10 በመቶ በሚል ተመዝኖ እንደሚከፋፈል አመልክተዋል፡፡
የአዲሱ ቀመር ችግር ምን እንደሆነ ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረበው ጥያቄ በተሰጠው ምላሽ፣ ቀመሩን እንዳለ እንውሰደው ከተባለ ለአንዳንድ ክልሎች ላይ ጫና እንደሚፈጥር፣ አንስተኛ የሕዝብ ቁጥር ያላቸው ክልሎች ተጨባጭ ሁኔታ አለመተንተኑና በአብዛኛው ለሕዝብ ቁጥር ያደላ በመሆኑ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
ስለዚህ ቀመሩ እያንዳንዱ ኢትዮጵያ ባለበት ቦታ የመንግሥት አገልግሎት ያግኝ፣ አንድ ክልል ከሠራና የተሻለ ከሆነም ይቀነሰብህ የማይባልበት፣ ከአቅማቸው በላይ የልማት ስራ ለሚሰሩ ክልሎች ትኩረት የሰጥ የሚሉ መርሆችን እንዲያሟላ ተጨማሪ ጥናት ስለሚያስፈልገው የነበረውን ቀመር ይዞ መሄድ የተሻለ መሆኑ ተብራርቷል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ እስከአሁን የድጋፍ በጀት ማከፋፈያ ቀመር የሚሰራው ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር በመሆኑ ከአሁን በኋላ ጉዳዩ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ስለሆነና የአንድ ጊዜ ሥራ ብቻ ስላልሆነ በቀጣይነት በፌዴሬሽኑ ይህን የሚመለከት አንድ ክፍል እንዲቋቋም ምክር ቤቱ ወስኗል፡፡ |