የብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በድምቀት ተከበረ

 

የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ህዳር 29 ቀን ቋንቋና ባህላቸውን ለማበልጸግና ከብረት የጠነከረ አንድነት ለመፍጠር ቃል የሚገቡበት ዕለት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አስታወቁ።

 

የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ለመጀመሪያ ጊዜ ህዳር 29 ቀ  በአዲስ አበባ የስብሰባ ማዕከል ሲከበር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እንደገለጹት የእያንዳንዱ ብሔሮች፣ብሔረሰብና ሕዝብ ቋንቋና ባህሉ ተከብሮ እኩል መሆን ብቻ ሳይሆን ይህንን ጸጋና ሀብት እንደጉልበት ተጠቅሞ ጠንካራ አንድነት መፍጠር ይገባዋል።

 

ሕገ መንግስቱ ያረጋገጠውን የህዝቦች መብት እኩልነትና ዴሞክራሲና እንደ መሰላል ተጠቅመው ከድህነትና ከተመፅዋችነት ለመውጣት የሀገሪቱ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቃል የሚገቡበትን ቀን እንደሆነም ገልፀዋል።

 

ጠቅላይ ሚስትር መለስ እነዚህ የተለያየ ባህልና ታሪክ ያላቸው ሕዝቦች የጋራ ክዳቸውን አስተባብረው አንድነቷ የተጠበቀ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሰፈነባትና ከኃቀርነትና ከድህነት የተላቀቀች አገር በመገንባት የሰላም የዴሞክራሲና የልማት ትግላችንን ማሣካት አለብን ብለዋል።

 

የፌዴሬሽን ምክረ ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ደግፌ ቡላ በበኩለላቸው የኢትዮጵያ አንድነት ሰላምና መረጋጋት ከኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እኩልነትና ነፃነት ተነጥሎ እንደማይታይ አመልክተው የበዓሉ መከበር እሰየው ቢባል እንጂ አስፈላጊ አይደለም ሊባል እንደማይችል ገልጸዋል።

 

አንዳንድ ወገኖች የባለብዙ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች አገር መሆንን እንደ ክፉ ዕጣ እኩልነትና ነፃነትን ደግሞ የአገር አንድነት ስጋት አድርገው ሲረዱና ሲያስረዱ መኖራቸውን አፈ ጉባኤው ተናግረዋል።

 

ከዚህ ቀደም የነበሩት የየሥርዓቱ አገዛዞች አንዱን ብሔር የበላይ ሌላኛውን የበታች እንደሆነ አድርገው በማቅረብ ለሥልጣን እድሜ ማራዘሚያነት እንደተጠቀሙበትም አስታውሰዋል።

 

መላው የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች መብታቸውን ለማስከበር ከኢህአዴግ ጎን ተሠልፈው ጭቆናና ባርነትን ለመጣል ሰፊ ትግል ያደረጉትና የተሳካ ውጤት ማስመዝገብ የቻሉት ያለፉት ገዢዎች ሥለጣንን ለማራዘም የነደፉትን ስልት ጠንቅቀው በማወቃቸው ነው ብለዋል።

 

በበዓሉ አከባበር ላይ የተገኙት ከ63 በላይ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ተወካዮች  ያቀረቡትን ትርዒት በሥነስርአቱ ላይ የተከኙት የክብር እንግዶች ተከታትለውታል።

 

ከወጣቶች ህፃናት ቲያትር ቤት የተገኙ የነገው ሀገር ተረካቢ ሕፃናት በተለያዩ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች አልባሳት አሸብርቀው የሕብረት ዝማሬ አቅርበዋል። ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሕገ መንግስቱን ለማፅደቅ ከተለያዩ አካባቢ ሲጠሩ የነበራቸውን ስሜትና አፅድቀው ሲመለሱ ያሳዮት እርካታ የሚያንፀባርቅ ትርዒትም ለእንግዶቹ አቅርበዋል። ለኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ማንነትና ባህል መታወቅ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረከቱ ግለሰቦችነና ድርጅቶችም አቶ ክፍሌ ወዳጆ ደራሲ ፍቅረ ማርቆስ ደስታ ከግለሰቦች ኢህአዴግ፣ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከልና ሰዎች ለሰዎች ከድርጅት ተሸላሚ ሆነዋል።

 

የብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በድምቀት ተከበረ