የኢትዮጵያ
ሕዝቦች ተቻችሎና ተከባብሮ
የመኖር ባህል የሀገሪቱ
ዋነኛ እሴት
መሆኑን ፕሬዚዳንት ግርማ
አስታወቁ
ኢትዮጵያ የተለያየ ባህል፣ቋንቋ፣ሃይማኖት ሥነልቦና ያላቸው በርካታ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ተቻችለውና ተከባብረ የሚኖሩበት ሀገር መሆኗን የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ አስታወቁ። ይህ ተቻችሎና ተከባብሮ የመኖር ባህል የአገሪቱ ዋነኛ እሴት በመሆኑ የበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቀረቡ።
በስብሰባ ማእከል የተዘጋጀውን ሲምፖዚየም ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ ሲከፍቱ እንዳስታወቁት በየዘመናቱ በነበሩበት ፀረ ዴሞክራሲ ሥርዓቶች ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች የአኩልነት መብታቸው ተነፍጎ በገዛ ሀገራቸው እንደሁለተኛ ዜና ተቆጥረው ኖረዋል።
ያለፉት ጨቐኝ ሥርአቶች በተከተሏቸው የከፋፍለህ ግዛ መርሆች ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች እርስ በእርሳቸው ሲናቆሩና ሲናናቁ እንደነበር የጠቆሙት ፕሬዚዳንቱ ከዚህ አይነቱ ጭቆና ለመላቀቅ ባደረጉት የዘመናት መራራ ትግል አዲስ የዴሞክራሲ ሥርዓት እውን ለማድረግ መቻላቸውን ገልፀዋል።
በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች በተወካዮቻቸው አማካኝነት የሀገሪቱ የሥልጣን ባለቤት በመሆናቸው የግልና የወል መብቶቻቸውን መከበሩንና ሕገ መንግስታዊ ዋስትና ማግኘታቸውንም አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ሥርአትን የተከተለች ከመሆኗም በላይ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በየአካባቢያቸው ራስን በራስ የማስተዳደርና እስከመገንጠል ድረስ የሚፈቅድ ሕገመንግስታዊ መብት መጎናፀፋቸውንም ገልፀዋል።
ባለፉት ሥርዓቶች ተረሰተውና ተረግጠው የቆዩ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በአካባቢያቸው የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች ተጠቃሚ ከመሆናቸውም ባሻገር በቋንቋቸው መናገር መማር፣ባህልና ማንነታቸውም መግለፅ መጀመራቸውን የጠቁሙት ፕሬዚዳንቱ፣ ይህም ልማትን ለማፈጠን የተሻለ ሕይወት ለመምራት እንዳስቻላቸው ገልጸዋል።
ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በተወካዮቻቸው አማካኝነት በፌዴሬሽን ምክር ቤት በመሣተፍ መብቶቻቸውንና ዘላቂ ሕልውናቸውን የሚያስከብሩበት ደረጃ ላይ መድረሳቸውንም ጠቁመዋል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ዶክተር መሐመድ ሰርሃዬ በበኩላቸው ህዳር 29 ቀን በሕዝቦች ትግልና መስዋዕትነት ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ድል የተቀዳጁበት፣ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፓብሊክ ሕገ መንግስት የፀደቀበትና ለሰላም፣ለልማትና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አዲስ ምዕራፍ የተከፈተበት ታሪካዊ ዕለት መሆኑን ገልፀዋል።
በአሁኑ ወቅት በሶማሊያ እስላማዊ ፍርድ ቤቶች ኀብረት ሥር የተጠለለው አክራሪ ቡድን፣የኤርትራ መንግሥትና ለሀገሪቱ በጎ የማይመኙ ኃይሎች የኢትዮጵያን ሰላም ለማወክና ሉአላዊነቷን ለመድፈር የቃጡትን አደጋ ለመመከት ሁሉም ዜጎች መረባረብ እንዳለባቸው አመልክተዋል። የሀገሪቱን ሰላም በማስጠበቅ የተጀመረው የልማት ጉዞ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ዜጎች የበኩላቸውን አስተዋዕኦ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
በሲምፖዚየሙ በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ገፅታ ከብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ማንነት ከሕገ መንግሥት ወደ ሕገ መንግሥታዊነት የተሸጋገረ የሕዝቦች ሥርአት በሚሉ ርእሶች የተዘጋጀና ያለፉትን ዓመታት የፌዴሊዝም ጉዞ የሚገመግሙ ጥናታዊ ፅሁፎች ቀርበው በተሳታፊዎች ውይይት ተደርጎባቸዋል።
የተለያዩ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ተወካዮች በሲምፖዚየሙ ላይ ተሣታፊ ሆነዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢፌዴሪ ሕገ መንግስት በሕብረተሰቡ ዘንድ በቂ ግንዛቤ እንዲያገኝ የሁሉንም ርብርብና ቁርጠኝነት እንደሚጠይቅ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር አስታውቋል።
ሚኒስቴሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል አከባበርን አስመልክቶ በሲፖዚየሙ መዝጊያ ላይ እንደገለፁት የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች መብት ያስከበረው ህገመንግስት በአብዛኛው ህብረተሰቡ ዘንድ በቂ ግንዛቤ እንዲያገኝ የሁሉንም ህብረተሰብ የእለት ተእለት ርብርብና ቁርጠኝነት ይጠይቃል።
ህገመንግስቱ በአብዛኛው ህዝብ ዘንድ በጥልቀት የሚሰርፅበት ሁኔታ በመፍጠር ህዝቡ መብቱንና ጥቅሙን በሕጋዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ ብቻ በማስከበር የሕግ የበላይነት በማረጋገጥ ለዴሞክራሲያዊ እንደተሰጠውም ገልፀዋል።
በተለይም አዲሱ ትውልድ የሕገመንግስቱን ፅንስ ሃሳብ በትምህርትና በተለያዩ መንገዶች እየተረዳ ቢመጣም የኢትዮጵያ ሁሉም ዜጋ መብትና ጥቅሙን በህጋዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ ብቻ ማስከበር እንዳለበት አምኖ የሀገር ግንባታው አካል እንዲሆን የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን መከበር ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው ብለዋል።
የበዓሉ መከበር ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በፈቃዳቸው የመሰሩት ፌዴራላዊ አንድነትን በበለጠ እንዲጠናከርና ሥር እንዲሰድ ለማድረግና ዜጎች በእምነታቸው በቋንቋቸውና በባህላቸው ሳያፍሩ ህገመንግሰቱ ያስከበረላቸውን መብት በተግባር እንዲገልፁ እድል የፈጠረላቸው እንደሆነም ሚስትሩ ገልፀዋል።